Tuesday, June 9, 2015

ኑ እንግደል!

“ክፉ የሆነውን የሥጋ ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን፣ በሕይወት ትኖራላችሁ፤” አ.መ.ት
“በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።”ሮሜ 8፡13

“ኃጢአትን ግደለው አለበለዚያ ይገድሃልና” ጆን ኦዌን[1]
በ ዮ ሐ ን ስ  መ ሐ መ ድ 
ክርስቲያናዊ ኑሮ ከኃጢአት ጋር በሚደረግ ትግል የተሞላ ነው። ይህ ከኃጢአት ጋር የሚደረግ ትግልን ለመግለፅ ንሥሓ፣ ኑዛዜ፣ ፀፀትና ተመሳሳይ ፅንሰ ሃሳብ የያዙ ቃላት እንጠቀማለን። ጆን ኦወን ኃጢአትን “መግደል” ባለው መልኩ ይህን ትግል መግለፅ ግን፣ እምብዛም የተለመደ አይደለም። ምናልባት ሰው እንደመሆናችን መጠን ኃጢአት አብሮን የኖረ ነውና ግደሉት የሚለው ቃል የባዕድነት ስሜት ስላለው ይሆናል።  ነገር ግን ጳውሎስ “በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ” በማለት የክርስቲያናዊ ሕይወት ተስፋ ኃጢአትን በየዕለቱ በመጋደል ተግባር ላይ የተመሠረተ እንደ ሆነ በግልጽ ይነግረናል። እንደ ጳውሎስ አተያይ፣ አማኝ በሕይወት የሚኖረው፣ በመንፈስ ኃጢአትን በመግደል ነው። አማኝ ከኃጢአት ጋር የድርድር፣ ጣት በመቀሰር የማላከክ፣ እንዲሁም እውነት እንኳ ቢሆን “ሰው ሁሉ ደካማ ነው” በሚል ፈሊጥ ከኃጢአት ጋር በደባልነት ሊኖር አይገባም፤ ኃጢአት ሊገድለው የሚገባው ሞገደኛ ባላንጣው ነውና።
ግደሉት የተባልነው “የሰውነት ሥራ” ወይም “ክፉ የሆነው የሥጋ ሥራ” ክፋቱ አብሮን የመኖሩ ጉዳይ ላይ ነው። ይህ “ክፉ ሥራ” ተገልጦ የሚታየው ለግዚአብሔር መገዛት በተሳነው እኛነታችን ወይም “ሥጋ” ተብሎ በተገለጠው ማንነታችን ላይ ነው። ጳውሎስ በሮሜ ውስጥ “መንፈስ” እና “ሥጋ” ብሎ የሚገልጣቸው ግንኙነቶች የሰውን የተለያዩ ‘ክፍሎች’ (በተለምዶ መንፈስ፥ ነፍስ፥ሥጋ የሚባሉትን) በመከፋፈል ሳይሆን፣ በጥቅሉ ለእግዚአብሔር የተገዛ ማንነትንና ከእግዚአብሔር ጋር ጠላት የሆነውን ማንነት ለማሳየት ነው። ከዚህ የተነሣ በክርስቶስ በመሆን ከኃጢአት ኵነኔ ያመለጡትን (ሮሜ 8፥1)፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ በመሆን የክርስቶስ ወገን የሆኑትን (ሮሜ 8፥9)፣ በምድር በሕይወት እየኖሩ “በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም” ተብለዋል፤ ይህ ማለት ግን ክርስቲያን አሁን ፍፁምነት ላይ ደርሷል፣ የሥጋ ራዎች የሚባሉትም በሕይወቱ አይገለጡም ማለት አይደለም። ምክንያቱም እንደ ሥጋ ፍቃድ እንዳይኖር ትዕዛዝ በዕዳ መልክ ተሰጥቶታልና“እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ዕዳ አለብን እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም።” (ሮሜ 8፥12)። ይህንንም ዕዳ የሚወጣው “እንደ ሥጋ ፈቃድ” ባለመኖር ወይም ዘወትር በመንፈስ ቅዱስ ኃጢአትን በመግደል ነው። በመሆኑም እውነተኛ አማኝ “ኃጢአት አይቀሬ ነው” የሚለውን አስተሳስብ ትቶ፣ ኃጢአት “ጠላቴ፣ ያውም በጉያዬ ታቅፌው የምዞረው፣ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ እሳተ ጎመራ ነው” በማለት ኃጢአት በኑሮው ላይ ዐቅም የሚያጣበትን በመለጠቅም የሚሞትበትን ሁኔታዎች ሁሉ ይፈጥራል።
       ኃጢአትን መግደል ግን በግል ጥረት ወይም በጠንካራ የሰው ፍቃድ ላይ የተመሠረተ አይደለም። ሰው በተፈጥሮው በሥጋ የተገዛ ማንነት ስላለው፣ እግዚአብሔርን ከማስደሰት ይልቅ ጠላት መሆን ይቀለዋልና (ሮሜ 8፥8)። ጳውሎስ እየተናገረለት ያለው የሥጋ ሥራ ግድያ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የሚደረግ ነው። የክርስቶስ የመስቀል ሥራ ለአማኞች ከመቆጠሩ የተነሣ አማኞች  “ሥጋን ከክፉ ሥራው ጋር ቢሰቅሉትም” (ገላ 5፥24)፣ በዕለታዊ ኑሯቸው “በመንፈስ” የኃጢአትን ሥራ የመግደል ዕዳ አለባቸው (ሮሜ 83)። መንፈስ ቅዱስም ቤተ ክርስትያንን ለወንጌል ሥራ ከማስታጠቅ በተጨማሪ፣ ኃጢአትን ጕልበት የማሳጣት ሥራን በእያንዳንዱ አማኝ ውስጥ ይሠራል። የአማኝ ልጅነቱም ማስረጃ በዚህ መንፈስ ምሪት ውስጥ መሆኑ ነው።“በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ። በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ እነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና” (ሮሜ 814)። ይህ ጥቅስ በተለምዶ አማኞች በየዕለት ኑሯቸው የእግዚብሔርን ፍቃድ ለማወቅ ምሪትን የሚጠይቁበት ቢሆንም በሮሜ ምዕራፍ 8 ዐውድ ውስጥ አማኞች በመንፈስ ቅዱስ በተመራ ሕይወት ኃጢአትን ማሸነፍ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው። ኃጢአትን በመግደል ሥራ ውስጥ እግዚአብሔር ለራሳችን ጕልበት አሳልፎ አልሰጠንም፤ ነገር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ ክርስቶስን ያስነሣውን መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ በማድረግ፣ ዘወትር ኃጢአትን የመግደል ሥራን ይፈጽማል (ሮሜ 8፥9-11)።
በመጨረሻም ይህ በመንፈስ የሚደረግ ኃጢአትን የመግደል ተግባር፣ ፍፃሜው ጽኑ የሆነ የሕይወት ተስፋ ነው። ‘ምን ዐይነት ሕይወት ነው’ የሚለውን ጥያቄ አሁን ባንመልሰውም፣“ብትገድሉ...በሕይወት ትኖራላችሁ” የሚለው ተስፋ ሰላምንና ይተትረፈረፈ ሕይወትን የሚጠቀልል፣በመንፈስ ኃጢአትን በመግደል ድርጊት አማካይነት የሚፈጸም ነው (ሮሜ 8፥6)። በመንፈስ የሚመራና ገዳይ ኃጢአትን እያስታመመ የሚኖር ክርስትና ለአዲስ ኪዳን ባዕድ ነው። ጠላቱ ኃጢአትን እሹሩሩ የሚል፣ ኃጢአትም የለም በሚል ክህደት የሚኖር፥ እንዲሁም ኃጢአት ዋጋን አያስከፍልም የሚል ክርስትና “እንደ ሥጋ ፍቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና” የሚለውን ማስጠንቀቂያ የዘነጋ ነው(ሮሜ 813)። ስለዚህ ወገኖች ሆይ፣ ኑ ኃጢአትን እንግደል!  




[1] ይህ መጣጥፍ ጆን ኦወን መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ ላይ የተመሠረተ ነው። John Owen, Overcoming Sin and Temptation, ed. Kelly Kapic & Justin Taylor (Wheaton, IL: Crossway Books, 2006).